የፖለቲካ አመራሩ ለጤና መድህን ፕሮግራም ውጤታማነት መረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተጠየቀ::

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የገቢ አቅም መሠረት ያደረገ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና አግልግሎት ማስፈጸሚያ ላይ ከክልሉ ማዐጤመ ቦርድ አባላትና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ በየደረጃው ያለው አመራር ለጤና መድህን ፕሮግራም ውጤታማነት መረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
“የጤና መድህን ፕሮግራም ለህዝባችን ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠ መሠረታዊ የጤና አግልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጎላ አስተዋጽኦ አለው” ያሉት አቶ ነጋ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በቂ ሀብት ማከማቸት አስፈላጊ በመሆኑ ገቢን መሠረት ያደረገና ከገበያ ሁኔታና ጋር የተጣጣመ የክፍያ ስረዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ፈጥኖ በማረም ዜጎችን በተሟላ መልኩ የጤና መድህን መርሀግብር ተጠቃሚ ለማድረግ አዲስ አባል ማፍራትና ነባር አባላት እድሳት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባም ነው አቶ ነጋ የጠቆሙት።
መንግሥት እንደ ሀገር የዜጎች ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ነጋ አበራ በክልሉም ሰብዓዊ ልዕልና በማረጋገጥ ለዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ለጤናው ዘርፍ ተገቢው ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በክልሉ የዜጎችን ማህበራዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ለጤናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ የገለጹት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም የጤና መድህን መርሀግብር የጤና አግልግሎት ፍትሀዊነትና ተደራሽነት ያረጋገጠ ሰው ተኮር ፕሮግራም መሆኑን ነው የገለጹት።
በክልሉ 56 ወረዳዎች የጤና መድህን ፕሮግራም እየተተገበረ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢብራሂም በበጀት ዓመቱ የየጤና መድህን ጤና አግልግሎት ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ የጤና አግልግሎት ለመስጠት በቂ ቅደመ ዝግጅት መደረጉንና በዚህም የፕሮግራሙን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የክፍያ ስርዓት አቅምን መሠረት ባደረገ መልኩ ማሻሻል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ የክልሉ የጤና መድህን የቦርድ አባላትና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።
ዘገባው የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።