ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመስጠት ሞዴል ቀበሌዎችን ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠንክረው መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

የጌሻ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የ2016 ዓ/ም ዕቅድ ክንውንና የ2017 ዓ/ም 1ኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
የጌሻ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታከለ ዓለማየሁ እንደተናገሩት ፍትሃዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመስጠት በጤና ሞዴል ቀበሌዎችን ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት እጅ ለእጅ ተያይዘው መስራት አለባቸው ብለዋል።
አክለውም የአካባቢያችን ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ የምንችለው ይበልጥ በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ስራ በመስራት እንደሆነና ዘርፉን ለማሻሻል የማህበረሰቡን ንቁ ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ ስንችል ብቻ ነው ብለዋል።
የጤና ስራ በሰው ህይወት ላይ የሚሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታከለ በዕውቀት የበለፀገ የሰው ኃይል እና በተቋም ደረጃም የተሻሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ሁሉም ባለድርሻ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
የጌሻ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዝናይ ዓለማየሁ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት እንደተናገሩት የወረዳችን ጤና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት በጤና ሞዴል ቀበሌዎችን በመፍጠር የተጀመረውን ውጥን ዳር ለማድረስ ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክረው ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል።
አያይዘውም ኃላፊው በወረዳው የወባ በሽታ ሰርጭት ስጋት የሆነባቸውን አካባቢዎች በመለየት እና የበሽታውን ስርጭት የሚያባብሱ ተግዳሮቶችን ጊዜ ሳይሰጠው በማስወገድ ሊሰራ እንደሚገባና የጤና ኤክንስቴንሽን ስራን በማጠናከር ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት መስጠት አለብን ብለዋል።
መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ተቀርፆ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ወዲህ በጤና ዘርፍ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገበ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ አብዝናይ ተግባራትን በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ የጤና አደረጃጀትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም በ2017 በጀት ዓመት በጤናው ዘርፍ ላይ የሚፈፀመውን ተግባር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የውይይት መድረክ መሆኑንም ኃላፊዉ ጠቁመዋል ።
ዘገባው የጌሻ ወረዳ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ነው።