ከፍተኛ የደም ግፊት (Hypertension )
የደም ግፊት ምንድን ነው ?
ደም በደም ወሳጅ ቧንቧዎች(Arteries) ላይ የሚያሳድረው ግፊት ነው።
የደም ግፊት እንዴት ይገለጻል ?
ምሳሌ፦120/80
👉 ሲስቶሊክ የደም ግፊት፦ልብ ደም ለመግፋት በሚኮማተርበት ግዜ የሚኖረው የግፊት መጠን ነው።
👉 ዲያስቶሊክ የደም ግፊት፦ልብ ዘና(relax) በሚልበት ግዜ የሚፈጠር የግፊት መጠን ነው
ከፍተኛ የደም ግፊት የምንለው መቼ ነው ?
የደም ግፊታችን 140/90 እና ከዚያ በላይ ሲሆን ነው።
ጤነኛ የደም ግፊት የምንለው የደም ግፊታችን 120/80 በታች
120-139/80-89 ሲሆን ደግሞ ቅድመ-ከፍተኛ የደም ግፊት (Pre-hypertension) እንለዋለን
የከፍተኛ የደም ግፊት መንስዔዎች
👉 መንስኤውን መሰረት በማድረግ ከፍተኛ የደም ግፊት በሁለት ይከፈላል፦
1. መንስኤው የማይታወቅ ከፍተኛ የደም ግፊት(Essential /primary hypertension)
- ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መንስዔ የሌላቸው ሲሆኑ ምንአልባትም በአካባቢያዊና በዘር ውርስ ምክንያቶች(Environmental and genetic factors) ይመጣሉ ተብሎ ይታመናል።
- ከ80-95% ይይዛሉ
2. መንስኤው የሚታወቅ ከፍተኛ የደም ግፊት(Secondary hypertension)
- ሊታወቅ የሚችል ብሎም የሚታከም መንስዔ ያለው
- ምሳሌ ፦በኩላሊት ህመም አማካኝነት ሊመጣ የሚችል ከፍተኛ የደም ግፊት ተጠቃሽ ነው።
- ከ5-20% የሚሆነውን ይይዛሉ
ለበሽታዉ የሚያጋልጡ ምክንያቶች
📌 የእድሜ መግፋት ፦በተለይም እድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶችና ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች የመያዝ ዕድላቸው ይጨምራል።
📌 ዘር፦-ከፍተኛ የደም ግፊት ብዙን ግዜ ከነጮች በበለጠ በጥቁሮች(Blacks) ላይ የሚስተዋል ሲሆን የሚያስከትለው ጉዳትም ከፍ ያለ ነው።
📌 በበሽታው የተያዘ ሰው በቤተሰብ ውስጥ መኖር
📌 ከመጠን ያለፈ ውፍረትና የሰውነት ክብደት
📌 የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ
📌 ሲጋራ ማጨስ
📌 የአልኮል መጠጦችን ማዘውተር
📌 ከመጠን ያለፈ ጭንቀት
📌 ጨው የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ
የበሽታው ምልክቶች
👉 የከፍተኛ ግፊት በሽታ አብዛኛውን ግዜ ምልክት አያሳይም ስለዚህ ያለን ብቸኛው አማራጭ የክትትል ምርመራ ማድረግ ነው። ነገር ግን ግፊታችን ከመጠን በላይ ሲጨምር የሚከተሉትን ምልክቶች ልናይ እንችላለን
📌 ከፍተኛ የሆነ ራስ ምታት
📌 የእይታ ችግር
📌 የድካም ስሜት
📌 የደረት ህመም
📌 ለመተንፈስ መቸገር
📌 የልብ ምት መዛባት
📌 ልባችን ሲመታ ለራሳችን መታወቅ
📌 ራስን መሳት ወይም የሰውነት መንዘፍዘፍ
📌 የሰውነት መስነፍ ወይም መደንዘዝ
📌 ለማወራት መቸገር
📌 ማስታወክና ማቅለሽለሽ
📌 ደም የቀላቀለ ሽንት
መቼ የህክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል?
👉👉 ከላይ በዝርዝር የጠቀስናቸውን ምልክቶች ካስተዋሉ የህክምና ባለሙያ ማናገር ያስፈልጋል በተለይ ደግሞ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለቦት ካወቁ ባፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል።
የከፍተኛ የደም ግፊት መዘዞች
📌 የልብ ድካም
📌 ወደ ልብ ጡንቻዎች ደም የሚያዘዋውሩ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች መጎዳት( Coronary Heart Disease)
📌 በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ ችግር(Stroke)
📌 የኩላሊት በሽታ
📌 የደም የቧምቧዎች በሽታ (Peripheral Arterial Diseases)
የከፍተኛ የደም ግፊትን ለመከላከልና ብሎም ለማከም መከተል ያለብን የአኗኗር ዘይቤዎች
📌 ጨው የበዛባቸውን ምግቦች አለመመገብና የገበታ ጨው አጠቃቀማችንን መመጠን ይህም ሲባል በቀን ከአንድ የሻይ ማንኪያ ያልበለጠ ወይም ደግሞ ከ 2 gm ያልበለጠ መጠቀም
📌 አትክልትና ፍራፍሬ፤አነስተኛ ቅባት ያላቸውን የእንስሳት ውጤቶችን፣ጥራጥሬ ፣የአትክልት ዘይቶችን ማዘውተር የሚከር ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ጣፋጭ መጠጦችንና ምግቦች እንዲሁም ቅባት የሚበዛባቸውን ምግቦች አለማዘውተር ይመከራል
📌 ከአልኮል ነክ መጠጦች እራስን መቆጠብ
📌 ሲጋራና ሌሎች የትንባሆ ውጤቶችን ከማጨስ መቆጠብ
📌 የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ (ቢያንስ በቀን ለ 40 ደቂቃ ፤በሳምንት ከ5-7 ግዜ መካከለኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለምሳሌ እንደ ርምጃ ፣ዋና፣ሳይክል መንዳት፣ሶምሶማ የመሳሰሉትን ማለታችን ነው
📌 የሰውነትን ክብደት መቀነስና ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖረን ማድረግ
ስለከፍተኛ የደም ግፊት የተሳሳቱ አመለካከቶች
📌 ወፍራምና ከልክ በላይ የሰውነት ክብደት ያላቸው ሰዎች ላይ ብቻ የሚከሰት አድርጎ ማሰብ
📌 የሀብታም በሽታ ነው ብሎ ማመን
📌 ምልክት ካላሳየ በቀር በሽታው የለብኝም ብሎ ማመን
📌 በቤተሰብ ውስጥ በበሽታው የተያዘ ሰው ስለሌለ ብቻ እኔ ላይ አይኖርም ብሎ ማመን
📌 በእርግማን የመጣ በሽታ አድርጎ ማመን
📌 እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ላይ ብቻ የሚከሰት አድርጎ መቁጠር
📌 የባህል ህክምና ( ለምሳሌ ፦የግብጦ አረቄ ፣ ሞሪንጋ የመሳሰሉት ) ፈዋሽ አድርጎ መቁጠር
📌 ውፍረትንና ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደትን ጤናማ አድርጎ መቁጠር
📌 የገበታ ጨውን ብቸኛው የጨው ምንጭ አድርጎ መቁጠርና መሰል አጓጉል አስተሳሰቦችን ልናስወግድ ይገባል