የሐሞት ጠጠር (Cholelithiasis)

የሐሞት ከረጢት የሚባለው የሰውነት ክፍል ከጉበት ሥር የሚገኝ አነስተኛ ከረጢት ሲሆን ለምግብ መፍጨት ሂደት አስፈላጊ የሆነዉ የሐሞት ፈሳሽ የሚጠራቀምበት አካል ነው፡፡
የሐሞት ፈሳሽ ጨዋማ ንጥረ ነገሮችን ያዘለ ሲሆን የምንመገበዉን ቅባት እና ቫይታሚኖች እንዲፈጩ ያግዛል፡፡
የሐሞት ጠጠር እንዴት ይከሰታል?
የሐሞት ጠጠር በሐሞት ከረጢት ውስጥ ወይንም ሐሞትን ከጉበት ወደ አንጀት በሚወስዱት ቱቦዎች ውስጥ የጠጠር ክምችት ሲኖር ነዉ፡፡
ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ሁኔታዎች
• ከ40 – 50 የዕድሜ ልክ ውስጥ ያሉ ሴቶች
• ነፍሰ ጡር
• ዉፍረት
• ቅባታማ ምግቦችን ማዘዉተር
• ስኳር ህመም
• በአጭር ጊዜ ክብደትን መቀነስ ናቸዉ
የሐሞት ጠጠር ህመም ምልክቶች
ሐሞት የሚወጣበት ቱቦ በሐሞት ጠጠር በሚዘጋበት ጊዜ በቀኝ ጎናችን የላይኛው ክፍል ላይ እየመጣ የሚመለስ ወይም የማያቋርጥ የሕመም ስሜትን ያስከትላል፡፡
የሐሞት ጠጠር ሕመም ወደ ጨጓራ እና ወደ ቀኝ ትከሻና ጀርባ የመሠራጨት ባሕሪም አለው፡፡ የህመም ስሜቱ የቅባት እህል ከተመገብን በኋላ መባባስ ከጨጓራ ሕመም እንደንለየው ይረዳል፡፡
• ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
• ምግብ ያለመፈጨት እና የመክበድ ስሜት
• ማስገሳት
• ሆድ የመንፋት ስሜት
• የምግብ ፍላጎት መቀነስ
ከዚህ በተጨማሪ የሐሞት መተላለፊያ ቱቦ በሚዘጋበት ወቅት/ Obstructive jaundice:
• የዓይን እና የቆዳ ቀለም ቢጫ መሆን
• ሰውነት ማሳከክ
• የሽንት ቀለም ቢጫ መሆን
• የሰገራ ቀለም መቀየር
• በሰውነት ላይ ቀያይ ነጠብጣብ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
መፍትሔው
አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዓይነት የህመም ስሜት ስለማያስከትል የሕክምና ዕርዳታ ላያስፈልገዉ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሕመም ስሜትን ካስከተለ የቅባት ምግቦችን መመገብ ማቆም እና የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን መውሰድ ለጊዜው የሕመም ስሜትን ያስታግሳል፡፡ ዘላቂ መፍትሔውም ቀዶ ህክምና /cholecystectomy/ ነዉ።

Similar Posts