የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምንድን ነው? እንዴትስ ይተላለፋል?

በምሥራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪካ በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) በሽታ በመላው አፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መሆኑን የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅት የተከሰተው በሽታው ወረርሽን ከዚህ በፊት ካጋጠሙት ወረርሽኞች ሁሉ የበለጠ አደገኛ መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል። ለዚህም ምክንያቱ አሁን እየታያ ያለው የዝንጀሮ ፈንጣጣ አዲስ ዓይነት የበሽታው ዝርያ በመሆኑ ነው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) በሽታ የሚከሰተው ሞንኪፖክስ በተባለ ቫይረስ አማካይነት ነው ሲሆን፣ ይህም ጉዳቱ ዝቅተኛ ከሆነው የፈንጣጣ ቫይረስ ቡድን ውስጥ የሚመደብ ነው።

የሽታው ቫይረስ በመጀመሪያ ላይ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ከሰው እደ ሰው እየተሰራጨ ይገኛል።

በሽታው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በመሳሰሉ በአፍሪካ ዝናባማ ጥቅጥቅ ደኖች ውስጥ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ በተደጋጋሚ ያሚያጋጥም ነው።

በእነዚህ አካባቢዎች በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው የሚያዙ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በበሽታው ለህልፈት ይዳራጋሉ። ከ15 ዓመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ልጆች በበሽታው በአስከፊ ሁኔታ ይጠቃሉ።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምንድን ነው?

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በሁለት ዋነኛ የቫይረስ ዝርያዎች አማካይነት ሲሠራጭ ቆይቷል።

“ክሌድ 1” (Clade 1) የባለው የቫይረሱ ዓይነት በማዕከላዊ አፍሪካ በስፋት ይገናል። “ክሌድ 1ቢ” የተባለው ደግሞ አሁን እየተስፋፋ ያለ አዲስ ቫይረሱ ዝርያ ከመሆኑ በተጨማሪ በጣም አደገኛ ነው።

የአፍሪካ ሲዲሲ እንደሚለው ካለፈው ጥር መጀመሪያ አንስቶ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ባሉት ሰባት ወራት ውስጥ ከ14,500 በላይ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከ450 በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሞተዋል።

ይህም ካለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በሽታው ክስተት ጋር ሲነጻጸር የበሽታው መስፋፋት 160 በመቶ፣ የሞት መጠን ደግሞ በ19 በመቶ ጨምሯል።

ከሽታው ክስተት 96 በመቶው በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተመዘገበ ሲሆን፣ አሁን ጎረቤት ወደሆኑት እና የዝንጀሮ ፈንጣጣ እምብዛም ወደ ማይታወቅባቸው ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ተስፋፍቷል።

በአውሮፓውያኑ 2022 ቀለል ያለው እና በምዕራብ አፍሪካ የሚገኘው “ክሌድ 2” (Clade II) የተባለው የበሽታው ዝርያ በዓለም ዙሪያ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ነበር።

በወቅቱ በሽታው ቫይረሱ ተከስቶባቸው የማያውቁት የአውሮፓ እና የእስያ አገራትን ጨምሮ 100 በሚጠጉ አገራት ውስጥ ተከስቶ ነበር። ነገር ግን ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በመከተብ ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ውሏል።

 እስካሁን በየትኞቹ አገራት ተከሰተ?

በዲሞክራቲክ ኮንጎ ያለው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት እና ህክምና አቅርቦት ዝቅተኛ በመሆኑ የአገሪቱ የጤና ባለሥልጣናት የበሽታው ሥርጭት አሳስቧቸዋል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተመዘገበው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክስተት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ለዚህም አጣዳፊ የሕብረተሰብ ጤና ጥበቃ እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን፣ ግንዛቤ ለማስጨበጥም ሕዝባዊ ንቅናቄ እየተካሄደ ይገኛል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) በቀጠናው እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ በሽታውን ለመቆጣጠርና ማኅበረሰቡን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

የበሽታው ክስተት በምሥራቅ እና በመካከለኛው የአፍሪካ ክፍሎች እየስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የጤና ባለሥልጣናት የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ነው ሲሉ አውጀዋል።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ በተጨማሪ በኡጋንዳ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው በቅርቡ ይፋ ተደርጓል። ከኡጋንዳ በተጨማሪ ሌሎቹ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በኬንያ፣ በሩዋንዳ እና በቡሩንዲም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

የአፍሪካ ሲዲሲ እንዳለው አምና ከተመዘገበው የበሽታው ክስተት ቁጥር አንጻር የዘንድሮው በአንድ ከግማሽ ጨምሯል። የሞት ቁጥርም አምስት እጥፍ ሆኗል።

የበሽታው ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?

በቫይረስ አማካይነት በሚተላለፈው በዝንጀሮ ፈንጣጣ በተያዘ ሰው ላይ መጀመሪያ የሚታዩት ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ ጀርባ ህመም እና የጡንቻ ህመምን ያካትታል።

ትኩሳት ከተከሰተ በኋላ ከፊት ጀምሮ ቀሪውን የሰውነት ክፍልን የሚያዳርስ ሽፍታ የሚከሰት ሲሆን፣ በአብዛኛው በእጅ መዳፍ እና በእግር መረገጫ ላይ ይከሰታል።

በሰውነት ላይ የሚያጋጥመው ሽፍታ በጣም የሚያሳክክ እና የሚቆጠቁጥ ሲሆን፣ በተለያዩ የለውጥ ደረጃዎች ውስጥ አልፎ በመጨረሻም እብጠት በመፍጠር ኋላ ላይም ይከስማል። ቁስለቱም ጠባሳን ትቶ ሊያልፍ ይችላል።

በሽታው በአብዛኛው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ በራሱ የሚጠፋ ይሆናል።

በበሽታው የተያዘው ሰው ክፉኛ የተጎዳ ከሆነ ቁስለቱ አጠቃላይ ሰውነቱን፣ በተለይ አፍ፣ ዐይን እና የመራቢያ አካላት ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

በሽታው እንዴት ይሠራጫል?

ቤተ ሙከራ ውስጥ በሚደረግ ምርመራ የሚገኝ ቫይረስ ሲሆን፣ በሰውነት ንክኪ ይተላለፋል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወሲባዊ ግንኙነትን፣ የቆዳ ንክኪን እና በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ማውራትን ወይም መተንፈስን ጨምሮ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር በሚኖር የቀረበ ግንኙነት ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።

የበሽታው ቫይረስ ወደ ሰውነት በቆሰላ ቆዳ፣ በመተንፈሻ አካላት፣ በዐይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ በኩል ሊገባ ይችላል።

በተጨማሪም በቫይረሱ የተበከሉ የመኝታ አልባሳት፣ በልብሶች እና በፎጣዎች አማካይነት በሚኖር ንክኪ በሽታው ሊተላለፍ ይችላል።

ሌላኛው የበሽታው መተላለፊያ መንገድ ደግሞ ቫይረሱ ካለባቸው ዝንጀሮ እና አይጦችን ከመሳሳሉ ጋር የሚኖር ንክኪም አንዱ ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በዓለም ዙሪያ በበርካታ አገራት ውስጥ በተከሰተበት ጊዜ ቫይረሱ በዋናነት በወሲባዊ ግንኙነት በሚፈጠር ንክኪ አማካይነት ነበር የተሠራጨው።

በአሁኑ ወቅት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተከሰተው የበሽታው ወረርሽኝ የተስፋፋው በወሲባዊ ግንኙነት በሚፈጠር ንክኪ ሲሆን፣ ነገር ግን በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ቫይረስ ሊገኝ ችሏል።


እነ ማንን ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው?

አብዛኛው የበሽታው ክስተት የተመዘገበው ወሲባዊ ግንኙነት በሚፈጽሚ ሰዎች ላይ እና የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በሚፈጽሙ ወንዶች ላይ ነው። በተጨማሪም በርካታ የወሲብ አጋሮች ያሏቸው እና አዲስ የወሲብ አጋር የያዙ ሰዎች ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ነቻው።

የበሽታው ምልክት ካለባቸው ሰዎች ጋር የቀረበ ንክኪ ያላቸው የጤና ባለሙያዎች እና በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቤተሰቦች በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ።

ስለዚህም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ካለባቸው ሰዎች ጋር የሚኖር የቀረበ ንክኪን ማስወገድ እና በምንኖርበት አካባቢ በሽታው ከተከሰተ እጅን በሳሙና እና በውሃ መታጠብ ይመከራል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው በበሽታው ተይዘው የዳኑ ሰዎች ለ12 ሳምንታት ያህል ወሲባዊ ግንኙነት ሲፈጽሙ ኮንዶም መጠቀም ይኖርባቸዋል።

ህክምና አለው?

የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለማከም የተዘጋጀ ህክምና የታመሙ ሰዎችን ለማዳን በጣም ጠቃሚ ቢሆንም፣ ነገር ግን ህክምናው ምን ያህል ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ ውስን ጥናት ነው ያለው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝን በሽታውን በመከላከል መቆጣጠር የሚቻል ሲሆን፣ ይህንንም ለማድረግ ተመራጩ መንገድ የመከላከያ ክትባት መስጠት ነው።

በአሁኑ ጊዜ ሦስት በሽታውን መከላከያ የክትባት ዓይነቶች አሉ፤ ነገር ግን ክትባቶቹ የሚሰጡት ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቀረበ ንክኪ ላላቸው ብቻ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሰው መከተብ አለበት ብሎ አይመክርም።

ያሉት የክትባት ዓይነቶች አዲስ ከተከሰተው የበሽታው ዝርያ አንጻር ምን ያህል የመከላከል አቅም አላቸው የሚለውን ለማወቅ ተጨማሪ ሙከራዎች ማድረግ ኣስፈልጋል።

የዓለም የጤና ድርጅት መድኃኒት አምራቾች ያሏቸው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባቶች በሚፈለጉባቸው አገራት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ባያገኙ እንኳን ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ጠይቋል።

የአፍሪካ ኅብረት ለኮቪድ ተመድቦ ከነበረ ገንዘብ ላይ 10.4 ሚሊዮን ዶላር ለሲዲሲ በመስጠት የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ደግፏል።

Similar Posts